Skip to main content

Journalism in Ethiopia: Yesterday, Today and Tomorrow

Woubshet Taye Abebe is an Ethiopian journalist and writer. Prior to being convicted, along with three other journalists, under the Ethiopian terror act in 2011, he served as editor-in-chief of the Awramba Times, among other posts. He now works for the Gulale Post Magazine in Addis Abeba. Woubshet Taye Abebe’s article in this issue of PEN/Opp describes developments in journalism in Ethiopia – from the first printed newspaper, Aemro, to contemporary hopes and expectations in anticipation of the recently-signed agreement.

Credits Text: Woubshet Taye Abebe May 03 2019

የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ከመሰል የዓለም ታሪክ አኳያ ይገምገም ከተባለ በጣም ወጣት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በተለይ የሕትመት ሚዲያው ዘርፍ፤ በስልጣኔ ቀደምት ከሚባሉና የራሳቸው ፊደል ካላቸው አገራት ጋር ሲነፃፀር ጥያቄ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ እነዚያ ፊደላት በብራና ላይ እየተፃፉ ወደ ትውልድ ይተላለፉ ነበር፡፡ ስለዚህ ከጽሕፈት ታሪክ አንፃር ዛሬም ድረስ በአንዳንድ የምዕራባውያን ቤተ መዘክር ውስጥ ጭምር ያሉ የብራና ሰነዶች ዕውቀትን ባማከለና ስርዓታማ በሆነ መንገድ ቢመራ ለጋዜጠኝነት የመሰረት ድንጋይ የሚሆኑበት ዕድል ሰፊ በሆነ ነበር፡፡

ጋዜጠኝነት በኢትዮጵያ
ስለ ጋዜጠኝነት ወይም የፕረስ (ሚዲያ) ሙያና ሁለንተናዊ ክዋኔዎች ስናነሳ በአጠቃላይ የመገናኛ ብዙኃንን ማለትም የሕትመት ሥራንና ብሮድካስትን ያካተተ መሆኑን መግለጽ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ አውድ የነበረውን፣ ያለውንና ወደፊት ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን የምንዳስሰው ሁለቱን ዘርፎች በተቻለ መጠን እየዳሰስንና እየተነተንን መሄድ ከቻልን ብቻ ይሆናል፡፡

ምዕራፎቹ
ሀ - ‹የመጀመሪያው ትናንት›
*የጋዜጠኝነት ‹ሀሁ› በ19ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ
*በ20ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመርያ
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከ1890 – 1920 ያሉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ወርቃማ ዘመን ነበሩ፡፡ ከዚህ ወቅት ቀደም ብሎ በጋዜጦች ሕትመት ላይ ፎቶ ግራፍን ያካተተ ዜና መስራት መጀመሩ ለዓለም ታላቅ እመርታ የነበረበት፣ በጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ስማቸው ሲነሳ በአክብሮት የምንደመምባቸው እነ ጆሴፍ ፑሊትዘር፣ ዊሊያም ራዶልፍና ሎርድ ኖርክሊፍ የጋዜጣ ኢምፓየር የፈጠሩበት፤ ኢትዮጵያ ደግሞ በጣም ዘግይታ በዚሁ ወቅት ‹ሀሁ› ጋዜጠኝነትን የተዋቀችበት መቼት ነበር፡፡

በኢትዮጵያ የነገስታት ታሪክ ዓድዋ ላይ ባገኙት አንጸባራቂ ድል የሚጠቀሱት ቀዳማዊ አፄ ምኒልክ በሚዲያ ማቋቋም ታሪክ መሰረት የመጣሉን ዕድል አግኝተዋልም፣ ተጠቅመውበታልም ተብሎ ይታመናል፡፡ ይህ የሆነው በኢጣሊያ የቅኝ ግዛት መስፋፋት ጉዞ ወቅት በሁለቱ አገራት መካከል የፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ የኃይል አሰላለፉ ከአንዱ ወደአንዱ በሚዋዥቅበት መባቻ ላይ በወቅቱ በኢጣሊያ ቁጥጥር ስር ከነበረችው ‹ባሕረ ነጋሽ› (በኋላ ኤርትራ ተብላለች) አንድ ልሂቅ አምልጠው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው ነበር፡፡

እኒህ ልሂቅ ስማቸው ብላታ ገ/እግዚአብሔር ሲሆን በኤርትራ ‹ሐማሴን› በምትባለው ወረዳ ውስጥ ይኖሩ የነበሩና ቅኝ ግዛቱን አልቀበልም ብለው ወደኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ የአፄ ምኒልክ ከፍተኛ ባለስልጣን ወደነበሩት ወደ ሐረር ገዥ ራስ መኮንን ጉዲሳ በመሄድ አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ በቆይታቸውም ዓለም የደረሰባቸውን የሳይንስ ግኝቶች፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲና የንግድ ትስስር፣ እየገነኑ የሚወሱ የምዕራቡን ዓለም ፍልስፍናዎች፤ በአከባቢያቸው ለነበሩ መኳንንትና መሳፍንት ማጋራት ጀመሩ፡፡ ሁኔታው ጥሩ አጋጣሚ የነበረ ቢሆንም በዘመኑ በነበረው ኋላቀር አስተሳሰብ ድርጊታቸው በአዎንታዊነት አልተወሰደም ነበር፡፡ እንዲያውም በመኳንንቱ ዘንድ ብርቱ ጥላቻን አተረፉ፡፡ የሐረሩ ገዥ በበኩላቸው ለዘመናዊው አስተሳሰብ አክብሮት ቢኖራቸውም ተከታዮቸቸውን ማስከፋቱ አጣብቂኝ ውስጥ ሳይከታቸው አልቀረም፡፡ ቢሆንም ያልተጠበቀ አጋጣሚ በራሱ ጊዜ መጣ፡፡ ራስ መኮንን በድንገት አረፉ፡፡

የመጀመርያው ጋዜጣ - ‹አዕምሮ
ንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ ስለእኒህ አነጋጋሪ ልሂቅ በአጋጣሚው ይሰማሉ፡፡ ‹የምፈልገው የዚህ አይነቱን ሰው አይደል እንዴ?› በሚል ሁኔታ በአስቸኳይ ወደቤተ መንግሥታቸው እንዲያመጧቸው ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ ከመጡ በኋላም አዳዲስ አስተሳሰባቸውንና የሚናገሯቸውን ብስለት የተሞላባቸው ንግግሮች ሳያደንቁ አልቀሩም፡፡ ስለዚህም አንድ መመርያ ሰጡ፡፡

ብላታ ገ/እግዚአብሔር የሚናገሯቸውን ሳይንሳዊና ዓለም ዶርሶባቸዋል የተባለላቸው ግኝቶች በእጅ እየፃፉ ቤተመንግስቱ አከባቢ ለሚውሉ መኳንንቶች እንዲሰጡ ታዘዙ፡፡ አዳዲስ ዕውቀቶች ተከስተው በቤተመንግስት አካባቢ የተለየ አየር መንፈስ ጀመረ፡፡ ‹አዕምሮ› የሚለው ስያሜ የወጣውም ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደሆነ በወቅቱ ስለነበረው ሁነት ምልከታቸውን ያስተላለፉ ፀሐፍት ይገልጻሉ፡፡ ስያሜውን ያወጡትም ንጉሠ ነገሥቱ ነበሩ፡፡

የሆነ ሆኖ አንድ ችግር ነበር፡፡ ጽሑፉ የሚዘጋጀው በእጀ በመታገዝ ብቻ በመሆኑ የቅጅው መጠንም ሆነ የይዘት ስፋቱ ውስን ነበር፡፡ የሚዲያ ሥራ እዚህ የደረሰው የሚገኙ አጋጣሚዎችን ሁሉ በመጠቀም ነውና ሌላ መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ሳልባንዲአስ የተባሉ ግሪካዊ ደግሞ ሕትመቶች አንዴ ከተፃፉ በኋላ እንዴት እንደሚባዙ የሚያሳይ በወቀቱ ይሰራበት የነበረ ዘዴ ስለመኖሩ ለንጉሠ ነገሥቱ በመግለጽ 24 ገጽ ያለው ጋዜጣ እየታተመ ለመኳንንቱ ይከፋፈል ጀመር፡፡

የ‹አዕምሮ› ጋዜጣ ሳምንታዊ ሕትመት 200 ነበር፡፡ በወቅቱ በጣም ብዙ ተደርጎ ይገመት ነበር፡፡ እስከ 1898 ዓ.ም ድረስም በዚሁ ሁኔታ ቀጠለ፡፡ የተሻለ የተባለው የማተሚያ ማሽን የመጣው በዚህ ወቅት ሲሆን በ1900 ዓ.ም ደግሞ በዚሁ ‹ኢዴልቢ› የተባሉ የውጭ አገር ሰው ያስመጡት ማተሚያ ሐምሌ 17 ቀን 1900 ዓ.ም ‹ጎህ› የተሰኘች ጋዜጣ ዘመናዊ መልክ ይዛ ለንባብ በቃች፡፡

የቅኝ ግዛት ሙከራ
በወረራው ወቅት በስውር (Underground) የነፃነት ትግሉን የሚያቀጣጥሉ የሕትመት ውጤቶች፤ በአብዛኛው በበራሪ ወረቀት መልክ እየተዘጋጁ ይሰራጩ ነበር፡፡ የአርበኞችን ድሎች የሚዘክሩ፣ በውጭ ኃይል መገዛትን የሚቃወሙና ስለተቀናቃኙ ኃይል አሉታዊ ዘገባዎችን የሚያሰራጩ ‹ጥቁር አንበሳ› በተሰኘው አገር ወዳድ ምስጢራዊ ቡድን የሚረቀቅ፣ የሚታተምና የሚሰራጭ ነበር፡፡ በዘመናዊው የጋዜጠኝነት አስተምህሮ የዚህ አይነት ምስጢራዊ ሕትመቶች አምስተኛው የመንግስት አካል (The 5thState) ተብለው ይጠራሉ፡፡ ማሕበረሰባዊ ተጽዕኗቸው ከፍተኛ በመሆኑ ሕጋዊ የመንግስት ስልጣን ባለው አካል ተቀባይነት ባይኖራቸውም ማሕበረሰቡን የመምራት ሚና ስላላቸው ነው፡፡ አራተኛው የመንግስት አካል (The 4thState) የሚባለው ሕጋዊ መስመሩን ተከትሎ የሚሰራው ሚዲያ ሲሆን እንደ ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈፃሚው ሶስት መሰረታዊ የመንግስት መዋቅር ሁሉ በአራተኛ የመንግስትነት ዕሳቤ ይታያል የማለት ተጽኖአዊ ልኬት ስያሜ ነው፡፡

በወረራው ወቅት በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ውስጥ በፍፁም ሳይዘከሩ የማያልፉት ክብርት ‹ሲልቪያ ፓንክረስት› በእንግሊዝኛ የሚታተምና ኢትዮጵያ የተቃጣባትን የግፍ ወረራ የሚኮንን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰራጭ ‹The Ethiopian news› የተሰኘ ሰብስክራይብ የሚደረግ ጋዜጣ ነበራቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ይሳተፉባት ነበር፡፡

በማግስቱ- ቅኝ ግዛቱ ከሸፈ
ከኢጣሊያ የሁለተኛ ዙር የቅኝ ግዛት መክሸፍ በኋላ በወቅቱ የነበሩት (የመጨረሻው ሰሎሞናዊ ስርወ መንግሥት ንጉሠ ነገሥት) አፄ ኃ/ሥላሴ በመጀመርያ ያደረጉት ነገር ቢኖር ሚዲያውን በተቻለ መጠን ማስፋፋት ነበር፡፡ የዚህ ማሳያ ደግሞ ነፃነቱ እንደተገኘ ብርሃንና ሰላም መቋቋሙና በ1933 ዓ.ም ‹አዲስ ዘመን› የተሰኘው ዛሬም ድረስ ለንባብ እየበቃ ያለው መንግስታዊ ጋዜጣ መጀመሩ ነው፡፡ በተጨባጭ አይተግበር እንጂ ለመጀመርያ ጊዜ የጽሑፍ ሥራዎችና የግል መልዕክቶች ነፃነት በሕገ መንግስቱ ዕውቅና ያገኘው በዚሁ ወቅት ነበር፡፡ የንጉሠ ነገሥቱ የስደት ቆይታና የውጭው ዓለም ተሞክሮ የሚዲያን አስፈላጊነት በአጽንኦት ያስገነዘባቸው ይመስላል፡፡

ለ - ሁለተኛው ትናንት
ፊውዳላዊው ሥርዓት በታላቁ የ1966 ዓ.ም የኢትዮጵያ አብዮት ሲገረሰስ ለነፃው ፕሬስም፣ ለዴሞክራሲውም አዲስ ቀን ይመጣል የሚል ተስፋ ነበር፡፡ በተለይ የመድብለ ፓርቲ ፖለቲካ ዓይነት የፓርቲዎች አደረጃጀት ይታይ የነበረ ሲሆን ጠንካራ የተባሉት የፖለቲካ ድርጅቶች በልሳኖቻቸው አማካይነት ፕሮግራሞቻቸውን እያተሙ ያሰራጩ የነበረ መሆኑና በኢሌክትሮኒክስ ሚዲያ አማካይነት ደግሞ ‹ኢማሌድሕ› (የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅቶች ሕብረት) የተባለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ በነፃነት ፕሮግራሞቹን ያስተዋወቀበት አጋጣሚ ተመዝግቧል፡፡ ወዲያውም ለ17 ዓመታት የዘለቀ ተመሳሳይ መዝሙር የሚዘምሩ የዝርው ሚዲያ ውጤቶች አየሩን ተቆጣጠሩት፡፡

ሐ - የቅርቡ ትናንት
ይህ ወቅት የሚሸፍነው የሥርዓት ለውጥ ከተደረገበት ከ1983 ዓ.ም አንስቶ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለ27 ዓመታት የለየለት የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ ስልታዊና ተከታታይ ጥቃት የመሰንዘር ተግባራት በመንግስት የተለያዩ ተቋማት ሲፈፀምበት የቆየውንና እስከ 2010 ዓ.ም አጋማሽ የተቆየበትን ጊዜ ነው፡፡ ይህም በሶስት ክፍሎች ሊታይ ይችላል፡፡

ሀ - ከ1985 – 1997 ዓ.ም
ወታደራዊው ሥርዓት በተደረመሰ ማግስት የመጀመርያው የነፃ ፕሬስ አዋጅ ወጣ፡፡ ይህን ተከትሎም ከዚያ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከ380 በላይ ጋዜጦችና መጽሔቶች ፈቃድ አውጥተው ለአንባቢዎች መድረስ ጀመሩ፡፡ የተለያዩ ኃሳቦች መንሸራሸር ጀመሩ፡፡ ይህ ሁኔታም በባሕሪው ዴሞክራሲያዊነት ያልነበረውንና በሃሳብ የበላይነት ሳይሆን በጠመንጃ አፈሙዝ አሸናፊነት ወደስልጣን የመጣውን ስርዓት አርበደበደው፡፡ ስለዚህም የተለያዩ ክሶችን፣ ዛቻዎችንና ስልታዊ ጫናዎችን በማድረግ በርካታ ሚዲያዎች ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ፣ ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ ወይም በሙያቸው እንዳይቀጥሉ ተደረጉ፡፡

ለ- ከ1997 – 2002 ዓ.ም
ይህ የአምስት ዓመታት ጊዜ በኢትዮጵያ የፕሬስ ታሪክ ውስጥ ሁለት ዓይነት አሻራ ጥሎ ያለፈ መሆኑን ዘርፉን በቅርበት የመረመሩ ሁሉ የሚስማሙበት እውነታ ነው፡፡ የመጀመርያው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ምርጫ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሻለ ዝግጅትና መተባበር ስለተሳተፉበት ሰፊ የሚዲያ ሽፋንና የሕዝብ ትኩረት የሳበ መሆኑ ነው፡፡ ለሕትመት ሚዲያው የእመርታ ጊዜ (Booming time) ስለነበር በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመረያ ጊዜ ከ100 ሺህ በላይ ቅጅዎች (copies) በአንድ ሕትመት እየታተሙ የተሰራጩበት ነበር፡፡

ከ1997 ዓ.ም ዋዜማ ጀምሮ እስከ 1998 ዓ.ም ጥቅምት ወር ድረስ ሙያዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ጥረት እናደርግ የነበርን ጋዜጠኞች ሃሳብ ያለገደብ የተንሸራሸረበትን ውብ ተሞክሮ የምናስታውሰውን ያህል በተቃራኒው በፕሬስ ነፃነቱም ሆነ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ላይ ያስከተለውን ውድቀት በከፍተኛ ሐዘን ለታሪክ እናስተላልፈዋለን፡፡

መጥፎው አሻራ በምርጫው ጦስ በጥቂቱ 194 ንፁሃን በአልሞ ተኳሾች የተገደሉበት፣ ነፃ ሚዲያው መታገዱና ጋዜጠኞቹ በእስር ተግዘው እስከ ዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት የተፈረደባቸው መሆኑ ነው፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ በነበሩት ወራትም የዚህን ጽሑፍ አዘጋጅ ጨምሮ በርካታ ጋዜጠኞች የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጧቸውን ጋዜጣዊ መግለጫዎች ታድመው ሲወጡ በዘፈቀደና በተከታታይ እየታገቱ ይደበደቡ፣ ካሜራዎቻቸውና መቅረጸ ድምጾቻቸው ይሰበሩ ወይም ይወሰዱባቸው የነበረ መሆኑ ነው፡፡ በማይታወቁ እስራ ቤቶችና ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ አይናቸው ተሸፎኖ ለቀናት መቆየት የተለመደ ነበር፡፡

በጫና የተከበበው አምባገነናዊ ሥርዓት ነፃ ሚዲያና ዴሞክራሲን በሕግ ሽፋን ለመቀልበስ በማሰብ መጀመርያ ‹የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000› የተሰኘ አፋኝና አደገኛ ሕግ አወጣ፡፡ ይህ ሕግ ሃሳብን በነፃነት በመግለጽ ተፈጥሯዊ መብት ላይ በትልቁ የተቃጣ የማናለብኝነት ጥቃት ነበር፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ‹‹የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነ ምግባር ደንብ›› የተባለ የፕሬስ አዋጁ የሚሰጣቸውን የይስሙላ ዕድሎች ሳይቀር የነጠቀ ሕግ ወጣ፡፡ ወደመጨረሻ አካባቢ የምንመለስበት ቢሆንም የተወሰኑትን ለማሳያነት ማቅረቡ ጥሩ ይሆናል፡፡

ሐ- ከ2002 ዓ.ም - 2010
አምባገነንነት ሄዶ ሄዶ የማስመሰያ ሽፋን ሳይቀር የማያስፈልገው ወይም የማይጠቅመው ደረጃ ላይ ይደርሳል፡፡ በዚህ ዕሳቤ መሰረት ከ2002 – 2010 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ የነበሩት ጊዜያት በሕግ ጭንብል ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማሞኘት እንደማይቻል የተረጋገጠበት ከመሆኑም በላይ የፕሬስ ነፃነት ሙሉ ለሙሉ የታፈነበት ወቅት ነበር፡፡ የተለየ ሃሳብ የነበራቸው ጋዜጠኞች በሙሉ ወይ ታስረዋል፣ ወይ ተሰደዋል፤ ወይም ሙያዊ ተግባራቸውን ለማቆም ተገደዋል፡፡

ዛሬ እና ነገ
ዛሬ የምንልበት አውድ በአጭሩ ከ2010 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ያሉትን የተወሰኑ የወራት ጊዜዎች ያካትታል፡፡ በእነዚህ ጥቂት ወራት የግፍ ሥርዓቱ በውርደት ከመንበሩ ላይ ወርዶ በሽግግር ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ሕዝብ የተቀናጀ ትግል ነፃ ወጥተዋል፡፡ ለበርካታ አስርት ዓመታት በስደት በውጭ አገራት የነበሩ፣ የትጥቅ ትግል ለማድረግ በረሐ የወረዱና ሌሎችም ወደአገራቸው በክብር ተመልሰዋል፡፡ በሚዲያ ሥራ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ያለምንም የተለየ መመዘኛ እየተሳተፉ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት ይንቀሳቀሳሉ፣ ቢሮዎች ይከፍታሉ፣ ሕዝባቸውን ያደራጃሉ፡፡

የዚህን ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢ ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላ የተካተቱበት የሚዲያ ሕግ ማሻሻያ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራዎች ተጀምረዋል፡፡

ሰፊ ጊዜ የወሰደ ውይይት፣ ምክክር፣ ጥናት፣ ግምገማና ተጨማሪ ጉዳዮች በተለያየ አቅጣጫ እየተፈተሹ ይገኛሉ፡፡ የሕጉን ማሻሻያ የተወሰኑ ክፍሎች ከዚህ ጽሑፍ ጋር ማያያዙ ስለነባራዊ ሁኔታችንና ነገ እናየዋለን ብለን ስለምናስበው የፕረስ ነፃነት መዳረሻ አመላካች ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡

የሚዲያ ሕግ ማሻሻያው
ቀደም ሲል ተጠቅሶ እንደነበረው የፍትሕና የሕግ ጉዳዮች አማካሪ ም/ቤት ከተቋቋመ በኋላ የምርጫ ሕጉ፣ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁና የመገናኛ ብዙኃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጁ የሕግ ማሻሻያ ያስፈልጋቸዋል በሚል ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት ሁኔታ ጥናትና ውይይት እየተካሄደባቸው ይገኛል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን እና የመረጃ ነፃነት አዋጁን አስመልክቶ የሚዲያ የሕግ ማዕቀፍ የጥናት ቡድን ሰፊ ጊዜ በመውሰድ በማሻሻያዎቹ ላይ እየሠራ ነው፡፡ የጥናት ቡድኑ በአገራችን ያለውን የሚዲያ ሁኔታ አስመልክቶ በደረሰበት ጥናት እንደገለጸው፡-

• የሀገሪቱ የሚዲያ ሕግጋት በተለይም የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ 590/2000፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999፣ እና የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 ዓለም አቀፍ ትችትን በማስተናገድ በአገራችን ገጽታ ላይ ጥቁር ጥላ ካጠሉ ሕግጋት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

• በዚህም ምክንያት በሥራ ላይ ያሉት ጥቂት ሚዲያዎችም አቅማቸው ደካማ ሲሆን በበቂ ጥናትና መረጃ ላይ የተመሰረተ የምርመራ ጋዜጠኝነት ፕሮግራሞችን አለማቅረብና የችግሮች መንስኤና መፍትሔን አለመጠቆም ችግርአለ፡፡ እራሳቸውን ሳንሱር ያደርጋሉ፡፡

• መንግሥት የመንግሥትና የግል ሚዲያን ሲያስተናግድ ግልጽ ልዩነት/አድልዎ ያደርጋል፡፡

ሲል ዝርዝር ጉዳዮቹን ያስቀመጠ ሲሆን በሌላ በኩል ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲታዩ በሚል የመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነጻነት አዋጅ 590/2000 የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/1999፣ እና የኮምፒዩተር ወንጀል አዋጅ ቁጥር 958/2008 ናቸው፡፡ ችግሮቹንም ለይቶ ለማየት ተሞክሯል፡፡ ሁኔታው በጅምር ደረጃ ተስፋ የሚሰጥ ሲሆን በአስቸኳይ ሆኖም በጥንቃቄ ለፍሬ በቅቶ ሚዲያዎች በተሻለ መልኩ መንቀሳቀስ መጀመር ይኖርባቸዋል፡፡

አትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች እንዲሁም በኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 29 በተረጋገጠው መሠረት ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በተሟላ መንገድ ሊያረጋግጥ የሚችል የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት፤ ማለትም

ከቁጥጥር ይልቅ ነፃነትን፣ ከገዳቢነት ይልቅ ፈቃጅነትን፣ ግልጽና ዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል የሚዲያ ተቋማት በመልካም አስተዳደርና ሰብአዊ መብት፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት ውስጥ ያላቸውን ሚና የሚያጎለብትና ዕውቅና የሚሰጥ ሚዲያዎች ከሕዝብ ጋር ያላቸውን አጋርነት የሚያጠናክር ውሱንና ተመጣጣኝ ቅጣቶች የሚያስቀምጡ ህጎችን ማውጣት አስፈላጊ ነው የሚል መዳረሻ ያለው ነው፡፡ እዚህ ላይ ቆመን ስለነገው መተለም እንችላለን፡፡

Like what you read?

Take action for freedom of expression and donate to PEN/Opp. Our work depends upon funding and donors. Every contribution, big or small, is valuable for us.

Donate on Patreon
More ways to get involved

Search