Skip to main content

The Dawn is Not Here

In 2011, award-winning Ethiopian journalist Reeyot Alemu was sentenced to fourteen years in prison for her writing, on an accusation of “terrorism”. Her crime was having written critical texts on political and social issues, focusing on poverty and equality. She spent five years in the infamous Kality prison. In this issue, she writes of the challenges facing Ethiopia in the coming years.

Credits Text: Reeyot Alemu May 03 2019

ርዕዮት አለሙ እባላለሁ ኢትዮጵያዊት ጋዜጠኛ ነኝ። ሙያዬን በስልጣን ላይ የነበረው አገዛዝ የሚያደርሰውን ግፍ ለማጋለጥ ተጠቅሜበታለሁ። ለዜጎች የሰብዓዊ መብቶች መከበር ታግዬበታለሁ። በዚህም ምክንያት ከአራት ዓመታት በላይ ለአስከፊ የእስር ህይወት ተዳርጌያለሁ። ለመታሰር ምክንያት የማይሆኑ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ነበሩና ስለእነሱ እየጻፍኩ መኖር እችል ነበር። እንዲያ በማድረጌ ከእስር ባመልጥም ከምፈራው የህሊና ፍርድ አላመልጥምና የተሻለውን መጥፎ መርጬ ድምጽ ላልነበራቸው ድምጽ ሆንኩ።

ከሁለት መጥፎ አንዱን እየመረጡ መኖር ዕጣፈንታዬ የሆነ ይመስላል። በእስር ቤትም የጠበቀኝ ይኸው ነበር። አገዛዙን ይቅርታ ጠይቆ መውጣት ወይም እንደ አገዛዙ ሰዎች አገላለጽ በእስር መበስበስ! ሁለቱም ያስፈራል፤ ይጨንቃል፤ ያማል። ከራሴ ጋር በብርቱ ተሟግቼ አሁንም አንዱን መረጥኩ። በእስር መቆየትን ምናልባትም እዛው እንዳሉ ለዘላለም ማሸለብን! የጡት ህመም እያሰቃየኝ ነበር። ህክምናም ጀምሬ ነበር። ይቅርታ አለመጠየቄን ተከትሎ ህክምናው ተከለከለ። ሌሎች በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንም አስተናግድ ጀመር። ይህ እንደሚመጣም የእስር ቤቱ ሃላፊዎች አስጠንቅቀውኝ ነበር። ግን ምን ማድረግ እችላለሁ? ይቅርታ ጠይቄ መውጣት መሸነፍ ሆነብኝ። ለዛውም ለምጸየፋቸው አምባገነኖች መሸነፍ! ደግሞስ ይቅርታ ጠይቄ እንደወጣሁ ትን ብሎኝ ብሞትስ? መኪና ብገጭስ? በቁጥጥሬ ስር ላልሆነች ህይወት ብዬ የምጠላውን ነገር ላለማድረግ ወሰንኩ። እናም አሰቃቂውን የቃሊቲ ኑሮ ወገቤን ጠበቅ አድርጌ እወጣው ጀመር። ከዛ አሰቃቂ ህይወት እወጣ ዘንድ ምክንያት የሆኑኝ በወቅቱ የአሜሪካ ፕት የነበሩት ባራክ ኦባማ ናቸው።

አገዛዙ የፕት ኦባማን የኢትዮጵያ ጉብኝት ምክንያት በማድረግ እኔንና የተወሰኑ ጋዜጠኞችና ጦማሪያንን ከእስር ለቀቀ።

ከእስር ብወጣም ልቤ ግን ታዋቂውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በርካታ በእስር ላይ ከነበሩ የመብት ታጋዮች ጋር እዛው ቀረ። እንደወጣሁ በእስር ላይ ስላሉ ንጹሃን ዜጎች ጉዳይ መጻፍ ጀመርኩ። አሜሪካ ከመጣሁ በኋላም በተለያዩ ስቴቶች እየዞርኩ በኢትዮጵያ ስላለው መጥፎ ሁኔታና ሊደረጉ ስለሚገባቸው እርምጃዎች በተለይ ለኢትዮጵያውያን ንግግር ማድረጌን ቀጠልኩ። ይሄን ሳደርግ ጡቴን ሰርጀሪ ካደረኩ ሳምንት እንኳ በቅጡ አልሞላኝም ነበር። በስደት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የመሰረቱት የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥንና ሬዲዮ (ኢሳት) ጣቢያ ባልደረባ በመሆንም በምወደው ሙያዬ የምጠላውን ጭቆና መታገሌን ተያያዝኩት።

ትግላችን ፍሬ ያፈራ መሰለ::የዲያስፖራው እገዛ ባይለየውም በዋናነት ሃገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት ትግል አገዛዙን ክፉኛ አዳከመው። ይህንን ተከትሎ ከአንዳንድ ግትር አባላቱ በቀር የኢህአዴግ አባላት ድርጅታቸው ሪፎርም ማድረግ እንዳለበት ከመተማመን ላይ ደረሱ:: በዚህም መሰረት የፓለቲካ እስረኞችን መፍታት ጀመሩ::የህዝቡ ትግል ግን ጋብ አላለም::የተቃውሞ ትኩረቱን ህወሃት ላይ በማድረግ ኢህአዴግን ከመሰረቱ አናጋው:: ይሄኔ የአራት ድርጅቶች ግንባር የሆነው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሁለት አባል ድርጅቶች ከእንቅልፋቸው ባነኑና የአገልጋይነት ሚናቸውን በመተው አለቃቸው ህወሃትን በአይናቸው ሙሉ ማየት ጀመሩ:: የተቃዋሚውን አጀንዳ ሙሉ ለሙሉ እንደራሳቸው አድርገው በማስተጋባትም ጣታቸውን ሲጨፈጭፉት ከኖሩት ህዝብ ጋር አብረው ህወሓት ላይ ጠቆሙ:: ኦህዴድ እና ብአዴን የፈጠሩት ትብብር ህወሓትን ከወሳኝነት ሚናው ገለል ማድረግ ቻለ ::የኦህዴዱ ሰው ዶር አቢይ አህመድ በዚህ መንገድ የጠቅላይሚኒስትርነቱን ቦታ ያዙ:: የበአለሲመታቸው ቀንም ከአንድ የኢህአዴግ አመራር ፈጽሞ በማይጠበቅ ሁኔታ ኢትዪጽያዊ ብሔረተኛ ተደርገው እንዲወሰዱ ያስቻላቸውን ንግግር አደረጉ:: ድርጅታቸው ኢህአዴግ ለሰራው ጥፋትም ይቅርታ ጠየቁ:: ብዙሀኑም አቅሉን እስኪስት በፍቅራቸው ወደቀ::

በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቲም ለማ በመባል ከሚሞካሹት በጣት ከሚቆጠሩ የኦህዴድና ብአዴን አመራሮች ጋር በፍጥነት የገቡበት ጭፍን ፍቅር መዳረሻ ያሳሰበን ጥቂት ሰዎች ድምጻችንን ለማሰማት ሞከርን:: ምላሹ ውግዘትና ስድብ ሆነ:: ውግዘቱ አገዛዙን አብረውኝ ሲቃወሙ ከነበሩ ጓዶቼ ጭምር ነበር ::

በእስር ላይ የነበሩ ንጹሀን ዜጎች መፈታታቸውን፥በፓለቲካ አቋማቸው ምክንያት ሀገራቸው መግባት የማይችሉ ዲያስፓራዎች ሀገር መግባታቸውንና ሌሎች መልካም ለውጦችን በመጥቀስም ከዚህ በላይ ምን እንዲመጣልኝ እንደምፈልግ ይጠይቁኝ ነበር:: ከይጠይቁኝ ነበር ሊያንጓጥጡኝ ይሞክሩ ነበር ብል ይቀለኛል:: እኔም የሀገር ጉዳይ ነውና ያለመታከት አቋሜን አስረዳና ስጋቴን ለማሳየት እጥር ነበር ::የህዝብ የተቃውሞ ማዕበል ገፍቶ እዚህ ያደረሳቸው ሰዎች ላይ ነገር አለሙን ጥሎ ከመቀመጥ ይልቅ ሰዎቹን በጥንቃቄ እየተከታተሉ በሀገራችን ፍትህና እኩልነት እስኪሰፍን ድረስ የድርሻን ማበርከት እንደሚገባ ወተወትኩ:: ይህ ሳይሆን ቢቀር የለውጥ ሀይል የተባሉት ቲም ለማዎች ወደሌላ ወደየትኛውም የሃይል ሚዛን ወዳደላበት ሀይል እንደሚያጋድሉ ጥርጣሬ ነበረኝ:: በቅርቡ ጥርጣሬዪ ስጋ ለብሶ ታየ::

በጫጉላው ሽርሽር ወቅት ስራቸውን ተግተው መስራት ያላቆሙት የኦሮሞ አክራሪ ብሔረተኞች የአሁኑን ኦዴፓ የቀድሞውን ኦህዴድ ፓርቲ እየተቆጣጠሩ ያሻቸውን ማድረግ ተያያዙት:: ከተለያዩ አካባቢዎች ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጽያውያን እንዲፈናቀሉም አደረጉ:: በዘውግ ብሔረተኝነት ተኮትኩተው ያደጉ ስራ አጥ ወጣቶችን በዘረኝነት ስብከት በመቀስቀስ ሀገራችንን ወደምድራዉ ሲኦል እየቀየሯትም ነው ::

ዶ ር አቢይ ከመጡ አንድም የታሰረ ጋዜጠኛ የለም ቢባልም እውነታው ግን ጋዜጠኞች ከመታሰር የበለጠ የሚያስፈራ ሁኔታ ውስጥ መኖራቸው ነው:: አንድ ማሳያ ብቻ ልጥቀስ:: በኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ቤታቸው እንዲፈርስባቸው የተደረጉ የለገጣፎ ነዎሪዎችን ቃለመጠይቅ ለማድረግ ወደስፍራው የተጓዙ የመረጃ ቲቪ ጋዜጠኞች በተደራጁ ወጣቶች ድብደባ ደርሶባቸዎል በተለይ ጋዜጠኛ ፋሲል አረጋይ ራሱን እስከመሳት ደርሶ ነበር ::የሚገርመው ድብደባው የተፈጸመው የለገጣፎ ፓሊስ ጣቢያ ፊትለፊት ፓሊሶች እየተመለከቱ መሆኑ ነው ፓሊሶቹ ከድብደባው ትንሽ ቀደም ብሎ የጋዜጠኞቹን ካሜራና ስልካቸውን ቀምተው ነበር:: የኦሮሚያ ክልል መስተዳድርን ማፈናቀል ለመሸፈን ፓሊሶቹና የተደራጁት ወጣቶች አብረው የሰሩበት የረከሰ አላማ ዘረኝነት መሆኑ ግልጽ ነው::

በፊት ለአንድ ጋዜጠኛ የሚያስፈራው እስር ቤት ዛሬ በመንጋ ፍትህ ተተክቷል:: መንግስት ያለ አይመስልም ኢትዮጽያዊነት ሱስ መሆኑን ተናግረው ኢትዮጽያውያን አንጀት ውስጥ የገቡት አቶ ለማ መገርሳም ከዚያ ተቃራኒ የሆነ መልዕክት በኦሮምኛ ያስተላለፉበት ቪዲዮ ህዝቡ ጋር ደርሶ ህዝቡ የተሸውደናል ስሜት ውስጥ ገብቷል:: በአንዴ ከመላዕክነት ወደ ሰይጣንነት ቀይሯቸዋል::በስልጣን ላይ ባለው ቡድን ሙሉ ለሙሉ ተስፋ ላለመቁረጥ አንድ ሰው ብቻ የቀሩት ሰውም ብዙ ነው::" "ዶር አቢይ ብቻቸውን ሆነው ነው፥አቅም አጥተው ነው" እያለ ራሱን ለማጽናናት ይሞክራል::

በሌላ በኩል"ድል ለዴሞክራሲ"በሚለው መፈክሩ የሚታወቀው ጋዜጠኛ እና አክቲቪስት እስክንድር ነጋ ወደዴሞክራሲ የሚወስደው መንገድ ጭላንጭል በአክራሪ የኦሮሞ ብሔረተኞች እንዳይጠፋ በሰላማዊ መንገድ በመታገል ላይ ነው:: አክራሪዎቹም ከጥፋት መንገዳቸው ሊያቆማቸው የሚሞክረው እስክንድርን ለማጥፋት እየዛቱ ነው::ለማንኛውም አልነጋም.

Like what you read?

Take action for freedom of expression and donate to PEN/Opp. Our work depends upon funding and donors. Every contribution, big or small, is valuable for us.

Donate on Patreon
More ways to get involved

Search